ናፍቆት
8 April 2008በእኔና አንቺ መሀል ወንዝ አለ መራራ፣
አላገናኝ አለኝ፣ ሆኖኝ ባላጋራ፤
ያዘኝ ደሀነቴ ድልድይ እንዳልሠራ፣
ዋኝቼ እንዳልመጣ ውሀ ልቤ ፈራ፡፡
አንቺ ወዲያ ማዶ፣ እኔ ወዲህ ማዶ፤
ልባችን በስሜት ርቀቱን ጥሶ፣ ገደሉንም ንዶ፤
ልዩነት ጅረትም ፈሶ፤ ወርዶ፤ ወርዶ፤
ቀን ሳይሞላ አይቀርም ለኛ ተዋኅዶ፡፡
እስቲመቸኝ ድረስ፣ እስቲመችሽ ድረስ እስከዚያ ልጨነቅ፤
እስቲመጣ ጊዜ ያንን ወንዝ የሚያደርቅ፣
የስሜቴን ምሥጢር እስተዚያ ልደብቅ፣
ያንን ፈገግታሽን እነዚያ ዓይኖችሽን በናፍቆት ልጠብቅ፡፡
መስፍን ወልደ ማርያም፤ እንጉርጉሮ፣ 1967
* * *
No comments yet