እግር ሲጥል
June 30th, 2008 by Brangoዕለቱ እሁድ ነው:: ጠዋት ከንቅልፌ ነቃሁና ገላዬን ተለቃልቄ ለሳምንት ከምቆይበት ከባለ አምስት ኮከቡ ሆቴል ፕሮቪደንስ ወጥቼ ቁርስ ለመብላት ወደ አንድ ካፌ አመራሁ::
***
የጠዋቷ ፀሐይ እየተንቦገቦገች ነው:: ራሷ ውበትን ተጎናጽፋ አካባቢውን ውበት አጎናጽፋዋለች:: በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2007 የሰኔ ወር መጨረሻ ላይ:: ፕሮቪደንስ ሮድ አይላንድ:: ፕሮቪደንስ ከቦስተን ማሳቹሴትስ ብዙም ርቃ የማትገኝ በተለይ ክረምት ላይ የምትደራ አሜሪካ ውስጥ የምትገኝ መካከለኛ ስፋት ያላት ከተማ ናት:: የብራውን ዩኒቨርስቲ በከተማዋ ውስጥ መገኘት ይበልጥ አድምቋታል:: ተማሪዎችም ብዙውን ጊዜ ሳትወድ በግድ ያደምቋታል—በረዶ እየዘነበም ቢሆን:: ተማሪነት ከትኩስ ወጣትነት ጋር ተዳምሮ ለከተማዋ ልዩ እስትፋንሷ ነው—ልዩ ውበቷ! ፕሮቪደንስ የጥበብ ሥራዎችም መፍለቂያ ናት:: ጥሩ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶችም አሉ:: ካፌዎችም እንዲሁ:- ከግዙፉ እስታርባክስ እስከ ትንጥዬዋ ካፌ ሉና! እሱ ትላልቅ ሆቴሎች ውስጥ ከመመገብ ትናንሾቹ ጋር መመገብን ይመርጣል:: ትናንት ቁርሱን ካፌ ሉና እራቱን ደግሞ ማይ ሊትል ፍሬንች ኮቴጅ በሚባል ሬስቶራንት ውስጥ ተመግቧል:: ምሳ ሥራ ቦታ ላይ ሆኖ ነው የበላው:: እሱ ለምሳ ብዙም አይጨነቅም:: ቀለል ያለ ሳንድዊችን ያዘወትራል:: ወይም ደግሞ የአትክልት ሳላድ:: የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ፕሮቪደንስ ውስጥ አላጋጠመውም:: እዚህች ከተማ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ያህል ይቆያል:: ከኮሌጅ ከተመረቀ ሁለት ወር ሊሞላው ጥቂት ቀናት ናቸው የቀሩት:: ዕድለኛነቱ ወዲያው እንደተመረቀ ሥራ ለመያዝ መቻሉ:: ለነገሩ ይህን ሥራ የጀመረው ተማሪ ሳለ ነበር—ኢንተርን በመሆን:: ሥራው ብዙ መጓዝን ይጠይቃል:: የሚሰራበት ካምፓኒ ሁሉንም ወጪ እየከፈለ ከቦታ ቦታ ይልከዋል:: የሱ ሀላፊነት ካምፓኒውን ማስተዋወቅና ከሌሎች ተመሳሳይ ካምፓኒዎች ጋር ግንኙነትን መፍጠር ነው:: ባለ አራትና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴሎች ውስጥ በየጊዜው ማረፍ ሳይሰለቸው አይቀርም:: ምንም እንኳ ባረፈበት ሆቴል ቁርስ መብላት ቢችልም ብዙን ጊዜ የትላልቅ ሆቴሎች ቁርስ አይመቸውም::
***
ሁለት ቀን ካፌ ሉና ቁርሴን ስለበላሁ ዛሬ ደግሞ እስኪ ሌላ ቦታ ልሞክር አልኩና ወደ ካፌ ላ ፍራንስ አቀናሁ:: የፈረንሳዮችን ቁርስ ናፍቄ ሳይሆን በቃ አዲስ ነገር ለመሞከር:: ፍሬንች ቶስት ከካፌ ሞካ ጋር አዝዤ ጥጉ ላይ ወንበር ስቤ ቁጭ አልኩ:: አይፖዴን ከኪሴ አወጣሁና “ቫዮለንትሊ ሃፒ” የተሰኘውን የብዮርክን ሙዚቃ ማዳመጥ ጀመርኩ:: ጠዋቱን እንዲህ ካልጀመርኩት አይቻልም:: ዕለቱ እሁድ ቢሆንም ከሁለት ሰዓት በሁዋላ ሃይለኛ ስብሰባ አለብኝ:: ማታ ስዘጋጅበት ነበር:: የፓወር ፖይንቴን ደጋግሜ አጥንቼዋለሁ:: የ20 ደቂቃ ፕረዘንቴሽን አቀርባለሁ ለተለያዩ የቢዝነስ ማናጀሮች:: ይህ ሥራ ምንም እንኳ ልቤ ፈቅዶት የምሰራው ነገር ባይሆንም ጥሩ ስለሚከፈለኝ ቀን ማታ አዘቦት ሰንበት ሳልል እለፋበታለሁ:: ፍላጎቴ ግን ያለው ሌላ ቦታ ነው::
ቁርሴን እየበላሁ የብዮርክን ሙዚቃ እየመላለስኩ አዳመጥኩት:: አንድን ዘፈን ከወደድኩት መላልሼ ማዳመጥ ደስ ይለኛል:: ስልችት ሲለኝ ደግሞ እርግፍ አደርገውና ለወር ለሁለት ወር ያን ዘፈን ዞር ብዬ አላየውም:: በጣቶቼ ክቡን ጠረጴዛ እየቆረቆረኩ ካፌ ሞካውን አጣጣምኩት:: ካፌ ሞካ በቅርቡ ፍቅር ካስያዙኝ ነገሮች መካከል አንዱ ነው:: የራሱ የሆነ ታሪክ አለው:: ዝርዝር ውስጥ አልገባም::
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ህይወቴን ለዘላለሙ የሚለውጥ ነገር ተከሰተ::
ከፊት ለፊቴ አንድ የፀሐያ መነጽር ያጠለቀ ጺማም ነጭ ቁጭ ብሏል:: ያዘዘው ዳቦና ውሃ ነው:: የሚገርም! አልኩኝ በልቤ:: ደረቁን ዳቦ እየቆረሰ ይበላል:: ቆይቶ ደግሞ በውሃ ያወራርደዋል:: አልፎ አልፎ ገልመጥ ያደርገኛል:: ብዙ ስላየሁት መሰለኝ:: “ማይንድ ዩር ኦውን ቢዝነስ!” ዓይነት ነገር ነው አስተያየቱ:: ሆኖም እሱን ከመታዘብ አልተቆጠብኩም:: በጣቶቼም የማዳምጠውን ሙዚቃ ምት እየተከተልኩ ጠረጴዛውን መቆርቆሩንም እንዲሁ:: በስተግራዬ ደግሞ አንድ ነጭና አንዲት ኬንያዊ የምትመስል ቆንጆ ልጅ ቁጭ ብለዋል:: ሁለቱም መጽሃፍ በጃቸው ይዘዋል:: ትኩስ ቡና ፉት እያሉ ይወያያሉ:: እሷ በቦዲና ፒጃማ ነው ያለችው:: ከንቅልፏ እንደ ነቃች ወደ ካፌው ያመራች ትመስላለች:: ጡቶቿ ቦዲዋን ቀደው ለመውጣት የሚታገሉ ይመስላሉ:: አፍንጫዋ ትንሽዬ ናት:: ጸጉሯ ድሬድ ሎክ ነው:: በስተቀኜ ደግሞ አንድ በጣም ወፍራም ነጭ ሴትዮ ትልቅ የአሳማ ሥጋ ያለበት ሳንድዊች እየገመጠች ነው:: ከበስተጀርባዬ ሁለት ኢትዮጵያዊያን ቁጭ ብለዋል:: ላናግራቸው አሰብኩና በወሬያቸው መሀል ጣልቃ ከምገባስ ይቅርብኝ ብዬ አለፍኳቸው::
ያ ዳቦ በውሃ ሲመገብ የነበረ በድሜው ገፋ ያለ ጺማም ነጭ ወደ ተቀመጥኩበት ጠረጴዛ መጣ:: አንዲት መጽሐፍ የሱሬው ኪስ ውስጥ ውትፍ አድርጓል:: ያናግረኝ ጀመር:: የሙዚቃ ማዳመጫውን ጆሮዬ ላይ ሰክቼ ስለነበር ምን እንዳለኝ አልሰማሁትም:: እናም ማዳመጫውን ከጆሮዬ ላይ ነቀልኩት:: “ይቅርታ አልሰማሁህም” አልኩት በፈረንጅኛ:: “ምን ዓይነት ሙዚቃ እንደምታዳምጥ ነበር የጠየቅኩህ” አለኝ መነጽሩን እያወለቀ:: በጥያቄው ግራ ብጋባም “ብዮርክን ነው የማዳምጠው” አልኩት:: “የአይስላንድዋን ንግስት?! በጣም ግሩም ዘፋኝ ናት:: አንተም ስሜታዊ ሆነህ በጣቶችህ የሐሳብ ፒያኖን እየመታህ እያዳመጥካት ነው:: ግሩም!” አለና መለሰልኝ:: “የሙዚቃ መሳሪያ ትጫወታለህ?” ብሎ ከጠየቀኝ በኋላ ወንበር ስቦ ቁጭ አለ:: የኔን ፈቃድ አልጠየቀም:: ጤነኛ ነው እንዴ ሰውየው? እያልኩኝ በሆዴ “አይ የሙዚቃ መሳሪያ አልጫወትም:: ነገር ግን ለመጫወት በጣም እፈልጋለሁ:: በህይወቴ በጣም የምመኘው ነገር ነው!” አልኩት:: “መጀመሪያ ምኞት ይቀድማል:: ምኞት የሁሉም ነገር በር ከፋች ነው:: ከዚያም እንግዲህ እንደባለቤቱ ሁኔታ ምኞት ወይ ይሳካል አልያም ምኞት ሆኖ እውነት ሳይሆን ይቀራል::” በማለት መለሰ:: “እኔም እንዳንተ እመኝ ነበር::” በማለትም ቀጠለ:: “ምን ዓይነት ምኞት?” ጠየቅሁት::
“ዌል … ልክ እንዳንተው የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ምኞት::”
“ምን ዓይነት የሙዚቃ መሳሪያ?”
“ፒያኖ!”
“ህምምም … ታዲያ ምኞትህ እውን ሆነልህ?”
“በሚገባ! አንድ ቀን ከአንድ ጀርመናዊ ጋር ተዋወቅሁኝ:: የት ተገናኘን መሰለህ? አንዲት ምናምንቴ ካፌ ውስጥ:: በዚያ ሰዓት እንደ አንተ አይፖድ የማዳመጥ እድሉ አልነበረኝም:: ሆኖም ካፌው ውስጥ ሲጫወት የነበረውን ሙዚቃ እያዳመጥኩ በጣቶቼ የምመገብበትን ጠረጴዛ ስቆረቁር ጀርመናዊው አስተዋለኝ:: እናም ቀረበኝ:: አነጋገረኝ:: ማን እንደ ሆነ ምን እንደሚሰራ ከገለጸልኝ በኋላ ህይወቴን ለዘላለሙ የሚቀይር ነገር አደረገልኝ:: ምኞቴ ተሳካ:: ህልሜ እውን ሆነ:: ጀርመናዊው ሰው ከሙዚቃ ጋር አስተዋወቀኝ:: ስሙ ፍራንዝ ሉድዊግ ይባል ነበር—ነብሱን ይማርና:: የፒያኖ ማስተር መሆኑን የተረዳሁት በሥሩ ትምህርቴን መከታተል ከጀምርኩ በኋላ ነበር:: ታዋቂ የፒያኖ ተጫዋችና የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ነበር:: ራሱን ሲያስተዋውቀኝ ግን ብዙም ስለ እውቅናው አልነገረኝም:: ህይወቱ ልታልፍ ስትል ቃል አስገባኝ:: ልክ እሱ እውቀቱን ለኔ እንዳጋራ ሁሉ እኔም ለአንድ ሰው እውቀቴን እንዳጋራ:: ያ እውቀቴን የማጋራው ሰው በአጋጣሚ የምገናኘውና የሌላ ሀገር ዜጋ ሆኖ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ያለው መሆን እንዳለበትም ገለጸልኝ:: የዛሬ 40 ዓመት ነበር ይሄ የተከሰተው::”
“በጣም የሚገርም ታሪክ ነው:: የየት ሃገር ሰው ነህ—ማለቴ ትውልድህ:: እዚሁ አሜሪካ ውስጥ ነው?”
“ኦህ ኖ … ፈረንሳይ ነው የተወለድኩት:: ጀርመናዊውን የተዋወቅሁት እንግሊዝ ውስጥ ነበር:: ያጋጣሚ ነገር ሆነና ወደዚህ ሀገር ፈለስኩ:: አንተስ የየት ሃገር ሰው ነህ?”
“እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ:: ግን ለጊዜው ነው እዚህ የምኖረው:: ለትምህርት ነበር የመጣሁት:: ትምህርቴን ጨርሼ አሁን በመስራት ላይ ነኝ—ለአንድ የማስታወቂያ ድርጅት::”
“በጣም ግሩም:: ቀጣዩ ዕቅድህ ምንድነው?”
“እርግጠኛ አይደለሁም:: ትምህርቴን የጨረስኩት በቅርቡ ነው:: አሁን በምሰራበት ሞያ የምቀጥል አይመስለኝም:: ፍላጎቴ ያለው ሌላ ቦታ ነው:: ሙዚቃ ላይ! በተለይም ስለፒያኖ መማር በጣም እፈልጋለሁ:: የሚያሳዝነኝ ነገር ግን የሙዚቃ ትምህርት ቤት መግባት የምችል አይመስለኝም ከዚህ በኋላ:: ላለፉት አራት አመታት ያጠናሁት የቢዝነስ ትምህርትን ነበር:: ሁለት የሙዚቃ ኮርሶችን ከመውስድ ውጪ ብዙም ስለሙዚቃ የማውቀው ነገር የለኝም:: እናም በዚህ ምክንያት ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የመግባት ህልሜ በጣም የሞተ ነው:: ነገር ግን ሙዚቃን ማወቅ ዛሬም ቢሆን ከልቤ የምመኘው ነገር ነው::”
“ብዙም ተስፋ አትቁረጥ:: እንዳልኩህ ሁሉም ነገር በምኞት ይጀምራል:: ዕድል ምኞትህን ለማሳካት የቤትህን ደጃፍ ስታንኳኳ በፍንደቃ ኖር ማለት ነው:: ምን ዓይነት ሙዚቃ ትወዳለህ?”
“እኔ በርግጥ ይህ ነው ብዬ የምለየው ሙዚቃ ባይኖርም ከክላሲካል ሙዚቃ የቤቶቨንን የሾፐንን እንዲሁም የኢትዮጵያዊቷን የእማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩን ሙዚቃ በጣም እወዳለሁ:: ከሌላ የሙዚቃ ዘርፍ ደግሞ የጃዝ የሬጌ የሳልሳ የሜሬንጌ የብሉና የአፍሮቢት እንዲሁም የኢንዲ ሙዚቃ ነብሴ ነው:: የተለያዩ ሀገሮች ሙዚቃንም ማዳመጥ አዘወትራለሁ — ለምሳሌ የመካከለኛው ምስራቅንና የህንድን ሙዚቃ:: የሀገሬ ሙዚቃ ደግሞ ከሁሉም በላይ ይስማማኛል::”
“ጥሩ ምርጫ ነው:: ሙዚቀኛ ለመሆን ብዙ የሚጎልህ ነገር የለም:: ተሰጦውም ሊኖርህ ይችላል:: ማን ያውቃል?! በተለይ የሀገርህን ሙዚቃ አብልጠህ መውደድህ ደግሞ ግሩም የሚያሰኝ ነው:: እማሆይ ጽጌ ያልካቸውን ሙዚቀኛ አውቃቸዋለሁ:: ማለቴ ሙዚቃቸውን አዳምጫለሁ:: ስራቸው ረቂቅ ነው:: የእሳቸውን እግር መከተል የምትፈልግ ከሆነ ከአንተ ፈቃድ ጋር ባስተምርህ ደስ ይለኛል::”
“አር ዩ ሲርየስ?!”
“በሚገባ! ብራውን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሙዚቃ ትምህርት አስተማሪ ነኝ:: የማተኩረው ክላሲካል ፒያኖ ላይ ሲሆን ሳክስፎንም አስተምራለሁ:: ፍላጎቱ ካለህ እኔ አንተን ለማስተማር ዝግጁ ነኝ::”
“ግን እንዴት ሊሆን ይችላል:: ለምን እኔ?”
“ዚስ ሜይ ሳውንድ ዊርድ:: ግን አየህ ያ መምህሬ ቃል አስገብቶኛል:: እስከዛሬ ብዙ ሰዎች አጋጥመውኛል:: አብዛኛዎቹ ሙዚቃ ለመማር እንደሚፈልጉ ቢገልጹልኝም በቃላቸው ጸንተው አላገኘሁዋቸውም:: እስከዛሬ ብቁ የሆነ የፒያኖ ተማሪ አልፈጠርኩም:: ከኔ የተሻለ የፒያኖ ተጫዋች መፍጠር እፈልጋለሁ:: ሳይህ አንተ ጥሩ እጩ ትመስለኛለህ:: አላየኸኝ ይሆናል እንጂ እዚህ ካፌ ውስጥ ከገባህበት ሰዓት አንስቶ ሁኔታህን ስከታተል ነበር:: ጥቁር ብትሆንም የኔን ወጣትነት በጣም ነው ያስታወስከኝ:: እንዳንተ ቀጠን ያልኩ ነበርኩ:: ጠረጴዛ መቆርቆር በጣም እወዳለሁ:: ቁርስ ላይ ፍሬንች ቶስትና እና ካፌ ሞካ ነበር የማዘወትረው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ:: ዛሬ ግን ሁኔታዎች ተለውጠው ደረቅ ዳቦ እመገባለሁ:: ኤንዌ ኢፍ ዩ አር ሲርየስ ቱ ለርን ሚውዚክ ማይ ዶር ኢዝ ኦፐን ፎር ዩ:: ማይ ዋፍይ ዊል ቢ ቬሪ ግላድ ቱ ሲ ዩ ኤንድ ጌት ቱ ኖው ዩ:: ሳራፊና ትባላለች:: ከደቡብ አፍሪካ ነች:: የቤት ቁጥራችን ይኸውልህ:: ካም ሲ ኣስ ኦር ጊቭ ኣስ ኧ ኮል::” ብሎ ካርዱን ሰጥቶኝ ተሰናብቶኝ ወጣ::
ግራ የሚያጋባ ነገር ሆነብኝ:: እሺም እምቢም የማይሉት ነገር:: አሁን ምን ላደርግ ነው? አንድን ነጭ አምኜ ሥራዬን ልተው? ፈርቼስ ደጅ አንኳኩቶ የመጣልኝን ዕድል ላልፍ? የትኛው መንገድ እንደሚያዋጣኝ በግልጽ አላውቅም::
***
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ እሱ በአንድ አቋም ጸና:: የሙዚቃውን ፕሮፌሰር ሄዶ ለማየት ወሰነ:: የጀመረውን የሥራ ኩንትራት እስኪፈጽም ድረስ ፕሮፌሰሩ በትዕግስት እንዲጠብቀውም ተማፀነው:: ፕሮፌሰሩ ፈቀደለትም::
አንዳንድ አጋጣሚዎች ይገርማሉ:: ከአንድ ዓመት በኋላ እሱ የሙዚቃ ተማሪ ሆኖ ትምህርቱን በመከታተል ላይ ይገኛል:: ቪዛን በተመለከተም ችግር የለበትም:: የተማሪነት የመኖርያ ፈቃዱ ተራዝሞለታል:: በቅርቡ እማሆይ ጽጌ ማርያም ገብሩን ለመገናኘት ወደ እየሩሳሌም ያቀናል:: ለማመን የሚያስቸግር እውነታ ማለት እንደዚህ ዓይነቱን ነው:: ላይፍ ኢዝ ፉል ኦፍ ሰርፕራይዝስ! የማይቻል ነገር የለም::